​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​
​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​​

The power of freedom and unity

 Ethiopian Air Force

  •       ​​​​​​​​​​​
                  


                                                                                                      

አውሮፕላን ጋር የቆየ የድብቅ ፍቅር እንደነበረኝ አስታውሳለሁ ። ገና ጨቅላ ታዳጊ ሆኜ ከኰተቤ አፋፍ ላይ አሻግሬ ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ግዙፍ አውሮፕላኖች ሲነሱና ሲያርፉ በርቀት ስመለከት ልቤም አብሯቸው ይነሳና ያርፍ ነበር ። ታድያ አንድ ቀን አምላክ ቢረዳኝ እኔም እንደ አንደኞቹ እሆናለሁ እያልኩ እመኝ ነበር .. በልቤ ።
አየር ኃይልን ከመቀላቀሌ በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበርኩ ። ወጣትነት ብዙ የሚታሰብበትና የሚታቀድበት እንዲሁም የሚመረጥበት ወቅት በመሆኑ እኔም ውስጤ ያለውንና የሚያስደስተኝን ሙያ መምረጥ እንዳለብኝ የሚያስጨንቀኝ ዕድሜ ላይ ነበርኩ ። አውሮፕላን በራሪ መሆንን ደግሞ ከኰተቤ አፋፍ ላይ ጀምሮ የልጅነት ሕልሜ ሆኗል ።
2000 ዓም የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምልመላ በተመሳሳይ ጊዜ ነበርና መ/ቤቶቹ የጠየቁትን መስፈርት በማሟላት ሁለቱም ጋ ተመዘገብኩ ። በመጨረሻ ግን የተዋጊ ጀት በራሪነቱ የወጣትነት ልቤን ገዝቶት ኖር አየር ኃይልን መረጥኩ ።
አየር ኃይል የተዋጊ አውሮፕላን በራሪ የሚኰንበት መ/ቤት እንደሆነ ከማሰብ ያለፈ ጠለቅ ያለ ዕውቀት አልነበረኝም ። በእርግጥ የመከላከያ አንዱ ክንፍ መሆኑ ቢገባኝም ከኰተቤ አፋፍ ላይ ዘወትር አሻግሬ ከምመለከተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙም ልዩነት ይኖረዋል ብዬ አላሰብኩም ። ይሁን እንጂ የልጅነት ህልሜ ውስጥ በራሪ መሆን በቅሏልና አየር ኃይልን በፍቅር ወድቄለት ተቀላቅዬው አረፍኩት ።
እንዳለመታደል ሆኖ አየር ኃይልን ከተቀላቀልኩ በኋላ የገጠመኝ የጠበቅኩት አልነበረም ። በዚህ ተቋም ውስጥ ካለው ፈታኝ የወታደራዊና የበረራ ስልጠና በላይ ከሙያው መስፈርት ወጣ ያለው (Unprofessional) የአስተዳደር ስልት ገና በጠዋቱ
ውስጤን ይቆጠቁጠው ጀመር ። አየር ኃይሉ ሙሉ በሙሉ በገዢው ፓርቲ አባላቶችና የስርዓቱ ታማኝ አገልጋዮች ቁጥጥር ስር ውሏል ። ይህ ወታደራዊ ተቋም ዋነኛ የስርዓቱ ክንድ እንዲሆን ይፈለግ ነበርና ትምህርቱና ብቃቱ ከነበራቸው ሙያተኞች ይልቅ የፖለቲካ ታማኞችን የሚያበረታታ አሰራር ጠንክሮ ይታያል ። ይህ ከሙያ ብቃት ይልቅ ፖለቲካዊ ወገንተኝነትን መሰረት ያደረገን አካሄድ ልቀበለው እንደማልችል ውስጤ እየነገረኝ ቢሆንም የበረራ ስልጠናውን በትጋት በመከታተልና ጥቂቶችና ብቃት ያላቸው በራሪዎች ብቻ በሚመደቡበት ተዋጊ ስኳድሮን በሚግ 23 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ላይ በመመደብ አገሬን በቅንነትና በጀግንነት ለማገልገል ከመጀመሪያው ረድፍ ተሰለፍኩ ።
ተወልጄ ያደግኩት በመዲናችን አዲስ አበባ ነው ። እንደሚታወቀው አዲስ አበባ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች በአንድነት ተቀላቅለው የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ የእኔ የዘር ሃረግ እንደ ጥያቄ ወደ ጭንቅላቴ መጥቶ አያውቅም ። እናም የኢህአዴግ የአገዛዝ ስልት ሊመቸኝ ባይችል አያስገርምም ። ይህ ዘርን መሰረት ያደረገው የፖለቲካ አካሄድ ያለመተማመንን ፣ ከዚያም መለያየትን ያበረታታል ከሚሉት ወገን ነኝ ። የእኔ ፍላጐት ደግሞ መለያየት ሳይሆን አንድነት ነው ። ያለመተማመንን አጥብቄ እጠላለሁ ። በዚህ አስተሳሰቤም ጓጉቼለት ምርጫዬ ያደረኩት የአየር ኃይል ሙያና የፖለቲካው መስመር ተለያይተውብኝ ምቾት ነሳኝ ።
ዛሬ ላይ ሆኜ ያለፈን ታሪክ ሳወሳ ቀላልና የዋዛ ሊመስል ይችላል ። እዚህ ለመድረስ ግን ብዙ ውጣ ውረድን አሳልፊያለሁ ። በተለይ ግፍና በደል እየበዛ ሲሄድና ህሊና በቃኝ ሲል ፣ ውስጥህ አሻፈረኝን ማንጐራጐር ይጀምራል ። ያኔ ነገሮች ሁሉ ይቀያየራሉ ። እኔም ጋ የሆነው ይኸው ነው ።
2005 ዓም ድንገት በአገራችን የፖለቲካ አካሄድ ላይ ለውጥ የሚያመጡ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀመሩ ። የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በመንግስት ሚዲያ በይፋ በአገራችን ጉዳዮች ላይ ሲከራከሩ እንዲታዩ ሆነ ። የተቃዋሚዎች በይፋ ወጥተው ሃሳባቸውን የመግለፃቸው ክስተትና የገዢው ፓርቲም ሆደ ሰፊ መሆን በአገራችን የዴሞክራሲ ጭላንጭል የታየበት መድረክ ሆኖ ተስተውሏል ።
በዚህ የክርክር መድረክ የኢሕአዴግ ድክመትና ያሉበት ስህተቶች ጐልተው የወጡበትና ሚዛኑንም ስቶ ሲውተረተር ማየት በእጅጉ የሚያስደምም ትዕይንት ሆነ ። እንዲዚህ አይነት ግልፅ የፖለቲካ አካሄድ በአገራችን የተለመደ አልነበረምና ሁኔታው የሕዝቡን ትኩረት ሳበ ። እኔም እንደ አብዛኛው የአገሬ ሕዝብ ክስተቱን በመመልከት በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እየመጣ ነው በማለት ደስ ብሎኛል ።
በዚህ የለውጥ ሞቅታ ውስጥ እያለሁ ድንገት ከነበርኩበት የሚግ-23 ቦምብ ጣይ ተዋጊ ስኳድሮን ተነስቼ ለሱ-27 ተዋጊ አውሮፕላን ስልጠና ወደ ውጪ መሄድ እንዳለብኝ ተነገረኝ ። ትዕዛዙ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ዓይነት ነበር ።


በወቅቱ የሚግ 23 ቦምብ ጣይ ስኳድሮን የአብራሪ አቅሙ እጅግ ውሱን ነው ። እኔና 4 የበረራ ባልደረቦቼ በስኳድሮኑ የበረራ ዝግጁነትና ከኤርትራ ጋር በማንኛውም ሰዓት ወደ ውጊያ ሊገባ ይችላል በሚል ሰበብ ከዋናው ቤዛችን ባህር ዳር ተነስተን መቀሌ ከትመናል ። በዚህ ቀውጢ ሰዓትና የአብራሪ እጥረት ካጠቃው ሚግ 23 ስኳድሮን ተነስቶ ለሱ 27 ስልጠና በሚል ሰበብ ከአገር ውጪ የመሄዱ ጉዳይ አነጋጋሪ ነበር ። ይሁን እንጂ ከፖለቲካው ትኩሳት መራቄ ቅር እያለኝም ቢሆን የመጣውን ወታደራዊ ትዕዛዝ ያለ አንዳች ማመንታት መቀበል ነበረብኝ ።
የስልጠናው ዕድል እንዴት እንደተሰጠኝ ፣ ማንስ እንደመረጠኝና በምንስ መስፈርት እንደተመረጥኩ የማውቀው ነገር ባይኖርም ፤ ሱ-27 አውሮፕላን በዘመናዊነቱና በውጊያ ብቃቱ ብዙ የተባለለት መሆኑ እያስደሰተኝና በአገራችን እየተነቃቃ ያለው የፖለቲካ ለውጥ ውስጤን እያሞቀው ወደ ቀድሞዋ የሶቭየት ሕብረት አካል ቤላሩስ ተጓዝኩኝ ።
በአካል ከቤተሰቦቼና ከአገሬ ብርቅም ከአገር ስወጣ የነበረው የአገራችን የፖለቲካ ምስቅልቅል እያሳሰበኝ ነበር ። በአገኘሁት መንገድ ሁሉ ሁኔታዎችን በቅርበት ለመከታተል መረጃዎችን ከድሕረ ገፆችና ከተለያዩ ሚዲያዎች እቃርም ጀመር ። ያ አዎንታዊ የሆነው የአገራችን ዴሞክራሲያዊ የምርጫ አካሄድ ለአገራችን ሰላም መስፈን በእጅጉ ተስፋ እንደሚሰጥ እያሰብኩ ነበር ። ግና ብዙም አልቆየም ። ኢህአዴግ ለሕዝብ የገባውን ቃል አጠፈ ።
ከምርጫው ውጤት በኋላ እየተደረገ ያለውና እየተሰማ የነበረው ውዝግብ ሰላሜን ነሳው ። ተስፋ እንድቆርጥና ለምን ? የሚል ጥያቄ እንዳነሳም አደረገኝ ።
መከላከያ ሰራዊቱ አገርን እንጂ አንድን ፓርቲ አገልጋይ አይደለም የሚለውን ዴሞክራሲያዊ መርህ ውስጤ ይቀበላል ።
ሰራዊት አገር የመጠበቅ እንጂ ዜጋውን በጭካኔ የመግደል ስልጣን እንደሌለው በሚገባ የማውቅ ሰው ነኝ ። በውስጤም ለምንድነው ሕዝብ የሚጨፈጭፍ ስርዓት የማገለግለው ? የሚል ጥያቄ ፈጠረ ። እስከመቼ ነው ሕዝብ መብቱን ሲጠይቅ መሳሪያ የሚደገንበት ? ይህ ለእኔ ከባድ ወንጀልና ግፍም ጭምር ነበር ። የዚህ ወንጀል አካል ፣ ተሳታፊና መሳሪያ መሆን ደግሞ ፈፅሞ አልፈልግም ። ወያኔ እየገባበት ካለው የወንጀል ማጥ በራሱ ይውጣ እንጂ አጋር ልሆነው አይገባም አልኩ ። በታሪክ ተጠያቂ ከመሆንና ወልዶ ያሳደገህ ሕዝብ ላይ እንደ መተኰስ የሚያሳፍር የወንጀል ጫፍ የለምና ከዚህ ስርዓት ፈፅሞ መለያየት እንዳለብኝ ወሰንኩ ።
ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንደሚያደርጉት በገሃድ በአደባባይ መቃወም አለብኝ ብዬም ለራሴ ቃል ገባሁ ። ይህንን ለማድረግ ስልጠናውን ማቋረጥ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ነበረበት ። ሕይወት ውሳኔ ከሌለበት ስኬታማ አይሆንምና እኔም ተቋውሞዬን “ሀ “ ብዬ ለመጀመር ውሳኔ ላይ ደረስኩ ።
በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያውያን በያሉበት ለተቃውሞ በመውጣት የዓለም መንግስታት በሕውሃት አገዛዝ ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርጉ የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ነበር ። የተቀሩት የስራ ባልደረባዎቼም እንደ እኔው ያስቡ ነበርና ይህ አስተሳሰብ የእኔ ብቻ እንዳልሆነ ሳይ ተበረታታሁ ። በሚገርም ሁኔታ ከአስር የስራ ባልደረቦቼ መካከል ስምንታችን በአንድ ዓላማ ስር መሆናችንን አረጋገጥኩ ።
[page2image22856] [page2image23024] [page2image23192] [page2image23360] [page2image23528] [page2image23696] [page2image23864]
መ/አ ፋሲል ማሞ ከሚ-23 ተዋጊ አውሮፕላኑ ጋር
እንቅስቃሴያችን በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት ስምንታችንም ተስማምተናል ። በምንም መልኩ ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባ እንቅስቃሴ ማድረግ የለብንም ። እንዴት ፣ ለማንና መቼ እጃችንን መስጠት እንዳለብንና አጋርነታችንን ለሕዝቡ በምን መልኩ መግለፅ እንዳለብን አጠናን ።
እጃችንን ለመስጠት ያሰብንበት ቦታ ዋና ከተማዋ ሚኒስክ ውስጥ ሲሆን ከመኖሪያ ከተማችን ራቅ ያለ ነበር ። የምንፈልጋቸው ቦታዎችም የሚገኙት ሚኒስክ ውስጥ ነው ። ስለዚህም ወደ ከተማዋ ተጉዞ መረጃ መሰብሰብ የግድ ነበር ።
ሚንስክን መጐብኘት የሚል ሰበብ ሰጥተን በመጓዝ የምንፍልጋቸውን ቦታዎች ሁሉ አጠናን ። ይህ የሆነው እጅ ከመስጠታችን ጥቂት ቀናት በፊት ነበር ። እንደ አጋጣሚ እኛ እጃችንን ልንሰጥ ስናስብና በአገር ቤት ደግሞ ከስራ ባልደረቦቻችን መካከል መ/አ በኃይሉ ገብሬና መ/አ አብዮት ማንጉዳይ በታጠቁት ሚ-35 ሔሊኰፕተር አዲስ አበባ ሰላማዊ ሕዝብ አናት ላይ እንዲበሩ የተሰጣቸውን ግዳጅ ተቃውመው ወደ ጅቡቲ የኰበለሉበት ወቅት አንድ ሆኖ ነበር ። በዚህም የተነሳ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ እየደወሉ
[page2image32008] [page2image32168]
PDF created with pdfFactory trial version www.pdffactory.com
[page2image33024]
እንቅስቃሴያችንን መከታተል በመጀመራቸው እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገባን ።
የአንድ ዘመን ወጣት ተዋጊ በራሪዎች
አወጣጣችንን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ የምንኖርበት ቤት በጥበቃ ስር መሆኑ ነው ። የከተማዋ ፖሊሶችም ያውቁናል ። በተጨማሪም እኛ እጃችንን ለመስጠትና ከለላ እስከምናገኝ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ጉዳዩ አገር ቤት ቢሰማና ያለንበት ቦታም ቢታወቅ ሊደርስብን የሚችለው ነገር ከባድ መሆኑ እሙን ነበር ። ቢሆንም ይህ ሁሉ አደጋ ያሰብነውን ከማድረግ ወደ ኋላ የሚያደርገን ባለመሆኑ ዕቅዳችንን ለማሳካት በቁርጠኝነት ቀጠልን ።
እጅ ከመስጠታችን አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሁለት ባልደረቦቻችንን አስቀድመን ወደ ሚኒስክ በመላክ ሆቴል እንዲይዙና በተቻላቸው መጠን ጠቃሚ መረጃዎችን እንዲሰበስቡ አደረግን ። የላክናቸው ጓደኞቻችንም በቀለጠፈ አኳኋን ነገሮችን አስተካክለውና የሆቴላችንን አድራሻ ደውለው አሳወቁን ። እኛም በከፍተኛ ጥንቃቄ መኖሪያ ከተማችንን በመልቀቅ ሊገጥመን የሚችለውን ማንኛውንም ፈተና በፀጋ ለመቀበል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አካባቢውን ለቀን በመውጣት ሚንስክ ገብተን አደርን ።
በማግስቱ ማልደን በመነሳት በቀጥታ ወደ አሜሪካን ኤምባሲ በማቅናት አምባሳደሩን ለማነጋገር እንዲፈቀድልን ጠየቅን ። ይሁን እንጂ አምባሳደሩን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ምክትላቸውን ለማነጋገር ተፈቀደልን ። ለአምባሳደሩ ተወካይ ተገቢውን ሰላምታ ከአቀረብን በኋላ አገራችን ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ግድያና ያለመረጋጋት ፣ በተጨማሪም እኛ እየወሰድን ያለውን ዕርምጃ ዘርዝረን በማስረዳት የአሜሪካ መንግስት የፖለቲካ ጥግኝነት እንዲሰጠን አበክረን ጠየቅን ።
ተወካዩም ኤምባሲው ጥገኝነት መስጠት እንደማይችልና በተባበሩት መንግስታታ የስደተኞች ፅ/ቤት (UNHCR) በኩል ማመልከት እንደሚገባን አሰራሩን ጭምር በታላቅ ትህትና በማስረዳትና የጉዳያችንንም ከባድነት በመገንዘብ በኤምባሲው ወጪ ታክሲ ተከራይተው ወደ ስደተኞቹ ፅ/ቤት እንድንሸኝ
አደረጉ ። በኤምባሲው ለተደረገልን መልካም መስተንግዶ በማመስገን በታክሲ ወደ UNHCR (አለም ዓቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ፅ/ቤት) አመራን ።
ዕለቱ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ጁን 20 ነበር ። ይህ ቀን ደግሞ የዓለም የስደተኞች ቀን እንደሆነ ይታወቃል ። እንደ ዕድል ሆኖም በዕለቱ ፅ/ቤቱ ክፍት ነበርና የስደተኞቹ ፅ/ቤት ሰራተኞች በትህትናና በአክብሮት ተቀብለው አነጋገሩን ። ስለ እኛም ከአሜሪካ ኤምባሲ ተደውሎ እንደተነገራቸው አሳወቁን ። የጉዳያችንን ከባድነት በመረዳታቸው ብዙ አላጉላሉንም ። እንዲያውም የUNHCR ዋና ዳይሬክተር የነበርንበት ከተማ ድረስ መጥቶ በመጐብኘት ለጉዳያችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶት የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገባልን ።
ከUNHCR ጋር ያለንን ጉዳይ በቀላሉ እንደጨረስን ወዲያው በጀርመን ድምፅ በኩል እርምጃችንን ለዓለም ሕብረተሰብ ለማሳወቅ ከሬዲዮ ጣቢያው ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ ተስማማን ። የኢሕአዴግ አገዛዝ በሕዝባችን ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያ በመቃወምና ለወገናችን ያለንን አጋርነት በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖችና ለዓለም ሕዝብ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ግልፅ አደረግን ። ከዚያም ጉዳያችንን በቅርበት ሆነን ወደምንከታተልበት ከተማ ተላክን ።
ከሰከነ የሕይወት መስመር በአንድ ጊዜ ወደ አደገኛና መጨረሻው ምን ሊሆን መገመት ወደማይቻልበት የሕይወት መስመር ወረድን ። የስደት ሕይወትም “ሀ” ብሎ ተጀመረ ።
ስደት ቤላሩስ ውስጥ እጅግ አደገኛ ነው ። በማንኛውም ደቂቃ አደጋ ሊደርስብህ ይችላል ። ለደህንነትህም ምንም ዋስትና አይኖርህም ። ስለዚህ በዚህ አደገኛ አኗኗር ውስጥ እያለን ወደ ቤላሩስ የኢሚግሬሽን ፅ/ቤት በመሄድ የጥገኝነት ጥያቄ አቀረብን ። ጥያቄያችን ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ከአንድ ወር በላይ እንደሚፈጅና ለደህነታችንም የ24 ሰዓታት ጥበቃ እንደሚደረግልን በመግለፅ ትንሽ እፎይ እንድንል አደረጉን ። ቀን ቀን ሁለት በደምብ የታጠቁ ፖሊሶች ፣ ማታ ደግሞ ሁለት ሲኒየር መኰንኖች ተጨምረው መኖሪያችንን በመጠበቃቸው ሰላማችን መለስ ቢልም በዓይነ ቁራኛ ስለሚከታተሉን እንቅስቃሴያችን ፈፅሞ የተገታ ሆነ ።
የስደት ኑሯዋችንን ከጀመርን ማግስት አንስቶ በሞስኰ የኢሕአዴግ አገዛዝ አምባሳደር የነበረው ጄ/ል አሳምነው በዳኔ እኛን ለማግኘትና ለማነጋገር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመረ ። በፍፁም ልናገኘው እንደማንፈልግ ብንገልፅለትም ጉትጐታውን ማቆም ባለመቻሉ ከማንኛውም የኢትዮጵያ ባለስልጣን ጋር አንዳችም ድርደር ለማድረግ ፈቃደኛ ያለመሆናችንን በፅሁፍ ለአምባሳደሩ አሳወቅን ። ጐን ለጐንም ተቃውሟችንን በተለያዩ ሚዲያዎች ደጋግመን ማሰማታችንን ቀጠልን ።
[page3image29408] [page3image29576] [page3image29744] [page3image29912]
PDF created with pdfFactory trial version www.pdffactory.com
[page3image30768]
የእኛ ቁርጠኛ ተቃውሞ ለአየር ኃይሉም ሆነ ለገዢው ስርዓት ታላቅ ውድቀት ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ደስታንና ብርታትን የፈጠረ ነበር ።
በወቅቱ የቤላሩስ ፕሬዝዳንት የነበሩት አሌክሳንደር ሉካሼንኰ ለስደተኞቹ ኰሚሽን ኃላፊ እኛ ቤለሩስ ውስጥ እስከአለን ድረስ ምንም ዓይነት አደጋ እንደማይደርስብን ቃል እንደገቡላቸው ተነግሮናል ። በተቃራኒው ግን የቤላሩስ ወታደራዊ አዛዦችና ኃላፊዎች በድርጊታችን ደስተኛ ባለመሆናቸውና ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራቸው የሚችለው ወታደራዊ የንግድ ግንኙነት አደጋ ላይ በመውደቁ ሊበቀሉንም እንደሚፈልጉ በሚያደርጉት ድርጊትና በንግግራቸው ለመረዳት ችለን ነበር ።
አንድ ወር በታጠቁ ጠባቂዎች ቁጥጥር ስር መዋልና ውሉ ባልታወቀ ሁኔታ ነፃነትን እንደማጣት አስከፊና አስጨናቂ ወቅት አይኖርም ። ስንወጣም ሆነ ስንገባ የምናደርገውን ማናቸውንም እንቅስቃሴ ለእነርሱ የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎብን ሳለ አንድ ወር ሞላንና የቤላሩስ ኢሚግሬሽን ባለስልጣናት በሚያሳዝን ሁኔታ ጉዳያችን ተቀባይነት ባለማግኘቱ ወደ አገራችን እንድንመለስ የሚያዝ ውሳኔያቸውን አሳወቁን ። እንደ እነርሱ ገለፃ በአገራችን ውስጥ ሰላም እንደሰፈነና መንግስትም በደል እያደረሰ አይደለም የሚል ድምዳሜ ጨምረውበታል ። ከዚሁ ውሳኔ ጋር ተያይዞም መኖሪያችን አካባቢ የነበረው ጥበቃ በዚሁ ቀን ተነሳ ። ይህ የቤለሩስ ባለስልጣናት ውሳኔ እጅግ ከፍተኛ ጥርጣሬ ላይ ስለጣለን ለ UNHCR ጉዳዩን በዝርዝር ስናስረዳቸው እነርሱም ድንጋጤ ላይ ወደቁ ።
የቤላሩስ መንግስትን ውሳኔ ተከትሎ ሊደርስብን የሚችለውን አደጋ መገመት ቀላል ነበር ። በላያችን ላይ አደጋ እያንዣበበ እንደሆነ ተረድተናል ። በወቅቱ የሕውሃት አገዛዝ ያደረገውን የምርጫ ውጤት ማጭበርበር በመቃወም ከአገር ወጥተን መቅረታችን እንዲሁም በታወቁ የውጪ ሚዲያ ተቃውሞዋችንን መግለፃችን ምን ያክል ገዢውን ፓርቲ እንደጐዳው ግልፅ ነበር ። ከዚያም በላይ አየር ኃይሉ በአንድ ጊዜ 8 ተዋጊ በራሪዎችን ማጣቱ ምን ያክል እንደሚጐዳው መገመት አያዳግድትም ። በአገር ውስጥ ያሉ የግል ፕሬሶች በእኛ ጉዳይ ላይ በሰፊው ይዘግቡ ስለነበር ስርዓቱን በእጅጉ እየጐዳው ነበር ። በመሆኑም የሕውሃት አገዛዝ የከፈለውን መስዋዕትነት ከፍሎ እኛን በእጁ ቢያስገባ እንደ ከፍተኛ ድል ይቆጠርለታል ። ይህንን ዕቅዱን ለማስፈፀም ደግሞ በጐን ከቤላሩስ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ጋር በድብቅ እየተዋዋለ መሆኑ ይሰማል ። የቤላሩስ መንግስት የጥገኝነት ጥያቄያችንን ውድቅ ማድረጉና የተመደበልን ጥበቃም በአስቸኳይ መነሳቱ ለኢሕአዴግ ባለስልጣናት ዕቅዳቸውን ለማሳካት አመቺ ሁኔታ ፈጠረላቸው ።
ምንም እንኳ ይግባኝ መጠየቅ እንደምንችል ቢገለፅልንም ጥበቃ አልባ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ለቀን በፍፁም
መንቀሳቀስ እንደማንችል መነገሩ ጥርጣሬያችንን ከፍ አደረገው ። በዓይነ ቁራኛ መከታተላቸውንም ተረድተናል ።
ወጣቱ ካዴት ፋሲል ከበረራ አስተማሪው ጋር
የመጣውን አደጋ በፀጋ ከመቀበል ውጭ በኢሕአዴግ ሴራ ላለመውደቅ ለራሴ ቃል ገባሁ ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአራትና አምስት ቀናት ውስጥ ከቤለሩስ አስገድደው ሊወስዱን ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ጉዳያችንን በቅርበት የሚከታተሉ በመላው ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች አሳወቁን ። መረጃውም ሞስኰ ውስጥ ከሚኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያኖች አማካኝነት እንደተገኘም ተነገረን ።
ዝርዝር ዕቅዱም ኢሕአዴግ አንቶኖቭ -12 ተብሎ የሚጠራውን ግዙፍ የዕቃ ማመላለሻ የአየር ኃይል አውሮፕላን በጥገና ስም ወደ ቤለሩስ ሊያመጣና እኛን በማሳፈን አስገድዶ በዚሁ ወታደራዊ አውሮፕላን ከቤለሩስ ይዞ መውጣት ነበር ። ለዚህ ግዳጅ የሚተባበሩ የቤላሩስ ወታደራዊ ጄነራሎች ዳጐስ ያለ የአሜሪካ ዶላርና ውድ ገፀ በረከት እንደሚቀርብላቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል ።
በወቅቱ ይህንን መረጃ የሚያቀርብልን ሰው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆኑና ምን ማድረግ እንደሚገባን ሲያማክረን ጭንቀቱን በድምፁ መቆራረጥ መረዳት ቀላል ነበር ። በተቻለ ፍጥነት አሁን ካለንበት አካባቢ እንድንሰወርና ወደ ጐረቤት አገር መሻገር እንዳለብን አሳሰበን ። ይሁን እንጂ ከአካባቢያችን ለመሰወርም ሆነ ወደ ጐረቤት አገር ለመሻገር የሚያስችለን ምንም የሚያፈናፍን ሁኔታ አልነበረም ። በራሳችን ለመደበቅም ሆነ ለመንቀሳቀስ አልቻልንም ። አማካሪያችን ግን ወደ ሩስያ ብንሻገር እዚያ ያሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያኖች ነፍሳችንን ሊታደጉንና ማናቸውንም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸው ሲነገረን ልባችን ትንሽ ተስፋን አጫረ ። ብርታትም አገኘን ። ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ደጐች ናቸው ። የእኛን ጉዳይ እንደራሳቸው አድርገው እየተከታተሉ ነው ። ይህ ሕብረትና ቁርጠኝነት እንደሚያድነን ተስፋ አደረግን ። ይህ
[page4image30000] [page4image30168] [page4image30336] [page4image30504]
PDF created with pdfFactory trial version www.pdffactory.com
[page4image31360]
ከየአቅጣጫው የሚመጣልን እገዛ ብርታት ሆኖን የእኛም እልህና ቁጣ የዚያኑ ያክል ሆነ ። የመጣው ይመጣታል እንጂ ሕውሃት እጅ በመግባት የሕዝባችን የትግል ወኔ ላይ ውሃ አንቸልስም ። መስዋዕትነት ከጠየቀ መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ ነን ብለን ለራሳችን ደጋግመን ቃል ገባን ።
በሌላ በኩል ደግሞ ከተጋረጠብን አደጋ ክብደት አንፃር የተነገረንን ሁሉ ለማመን እየተቸገርን ነበር ። ብዙ ኢትዮጵያውያን ሊረዱን ቁርጠኝነቱ እንዳላቸው ብናምንም ከምንሰማቸው መረጃዎችና ግርግሮች ጀርባ የሕውሃት እጅ ቢኖርበትስ የሚለውን አስፈሪ ጥያቄ ማናችንም መመለስ አልቻልንም ። ከሚያናግሩን ውስጥ አንዳቸውንም በአካል የምናውቃቸው አልነበሩምና ክፉ ብናስብ የሚፈረድብን አይደለም ።
ኢሕአዴግ ባለ በሌለ ኃይሉ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ከመረጃዎቹና በአካባቢያችን ከሚታዩት እንቅስቃሴዎች መረዳት ቀላል ነበር ። እኛን እየተከታተሉ ወሬ የሚያቀብሉት ሰዎች እንዳሉ በሁኔታዎች እየተረዳን ነው ።
በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ እያለን ሊረዱን የተዘጋጁትን ኢትዮጵያውያኖች ማንነት ሊያጣራልንና ልናምነው የምንችለውን በአካልም የምናውቀውን የመጨረሻ ሰው የውስጥ ጥርጣሬና ፍርሃታችንን በድፍረት ማማከር ነበረብን ። በምላሹም ከነማን ጋር በቅርበት መስራት እንዳለብን አቅጣጫ በማግኘታችን እፎይታን አገኘን ። ከሞስኰም ሆነ ከሰሜን አሜሪካ ሰብዓዊነትን መመሪያቸው ካደረጉ ወገኖቻችንንም ጋር በግልፅ ልባችንን ከፍተን መነጋገር ጀመርን ።
በወቅቱ አገራችን ውስጥ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ እየተደረገ ያለውን ግድያና እስር በይፋ ወጥተን በመቃወማችን የበርካታ ኢትዮጵያኖችን ልብ በመግዛት ከፍተኛ አክብሮትን ለግሰውናል ። ከመላው ዓለም በተለይም ሰሜን አሜሪካ ያሉ ወገኖቻችን በሃሳብም በገንዘብም ለአንዲት ደቂቃ እርዳታቸውን ሳያቋርጡ አብረውን የጭንቀቱን ጊዜ እየገፉ ነበር ። ወደ ሕውሃት እጅ መውደቁን ሁሉም በአንድነት ለማስቆም ደፋ ቀና ብለዋል ። ለዓለም ህብረተሰብ አቤት ለማለትና በሕውሃት አስተዳደር ላይ ጫና ለመፍጠር በሰላማዊ ሰልፍም ሆነ አስፈላጊ ናቸው ይሏቸውን ቢሮዎች እያንኳኩ ጉዳያችንን እንደጉዳያቸው አድርገው አከናውነዋል ። ለእነዚህ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን ዜጐቻችን የምንከፍለውና የምናመሰግንበት ቃላቶች ዛሬ ድረስ ያጥሩኛል ።
እነዚሁ ወገኖቻችን ለየዕለቱ መኖሪያችን የሚያስፈልገውን የመጠለያና የምግብ ወጪ ከመደጐማቸው ስራ ጐን ለጐን ከቤላሩስ በሰላም በመውጣት ወደ ሌላ ሁለተኛ አገር ለማሸጋገር የሕይወት አድን ግብረሃይል በማቋቋም ሌት ተቀን እየሰሩ ነበር ። ይህ ግብረሃል ሁኔታዎችን በከፍተኛ ሚስጢር በመያዝ ፣
በሚቻለው ፍጥነት ከአለንበት አደጋ በአስቸኳይ እንድናመልጥ የሚያደርግ ዕቅድ ዘረጋ ።
አሁን በፍፁም የሚባክን ጊዜ የለም ። እኛም ሆንን ወገኖቻችን ሌት ተቀን እየተዘጋጀንና ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ በሙሉ ተጠንቀቅ ላይ ሆንን ። የምናመልጥበት መንገድም አማራጩ እጅግ የጠበበ ፣ ቁርጠኝነትና በፅናት መቆምን የሚጠይቅ እንደሆነ ብንረዳም ያለ መጠራጠር ዝግጅታችንን ቀጠልን ። ከሁሉም በላይ የነበረን ጥበቃ በይፋ ተነስቷል ይበሉን እንጂ በተለያዩ ሁኔታዎች በድብቅ እንቅስቃሴያችንን ይቆጣጠሩ ነበር ።
ሞስኰ ካሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድ ነገር ተስማምተናል ፤ ይኸውም መኖሪያ ቤታችን መጠናት ነበረበት ። ይህንንም ጉዳይ የሚያከናውን ሰው ተልኰ ካሜራ መኖሩን ፣ መኖሪያ ቤታችን ምን እንደሚመስል ወጣ ገባውን አጥንቷል ። ምክንያቱም ከቤታችን መውጣት ባንችል እንኳ እቤት ድረስ ገብቶ ማዳን የሚል የመጨረሻ አማራጭ ስለነበረውም ጭምር ነበር ።
የሞስኰ አገር ወዳዶች ከሞስኰ ባለስልጣናት ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን የተቀሩትም በሞስኰ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ የሚደረገውን በቅርበት መከታተል የሚችሉ ነበሩ ።
የኢትዮጵያ ገዢዎችና የቤላሩስ ጄነራሎች እኛን ለመበቀል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በእነዚህ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥብቅ ክትትል ስር ወድቋል ። እነዚህ አገር ወዳዶች ደግሞ እኛን ሊረዱን ይችላሉ ለተባሉት አካላት በአስቸኳይ እየተደረገ ያለውን ያሳውቃሉ ። መልዕክቱን የሚቀበሉት ክፍሎች ደግሞ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ከፍለው እኛን ለማዳን ቅድመ ዝግጅታቸውን እየነደፉ ነበር ።
ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ነገር ግን ተከፍሏቸው መረጃዎችን የሚያጠናቅሩት ሰዎች ዱካችን በሚገባ እየተጠበቀ እንደሆነና መኖሪያችንም ዙሬያውን በካሜራ እንደሚጠበቅ አረጋገጡ ። ይህ መረጃ ለእኛ መድረሱ እጅግ ጠቃሚ ነበር ። በተቻለ መጠን ትኩረት ሳንስብ ተራ በተራ መኖሪያችንን መልቀቅ እንዳለብን ረድቶናል ።
አወጣጣችን ምን መምሰል እንዳለበት ፣ ከመኖሪያ ቤታችን ስንወጣ የምንሰጠው ምክንያት ፣ ስንት ስንት ሆነን እንደምንወጣ ፣ አለባበሳችን ምን መምሰል እንዳለበትና በመጨረሻም የመገናኛ ፣ የመሰባሰቢያ ቦታችን የት ሊሆን እንደሚገባውና የተቀሩትንም ጥቃቅን ነገሮች እንዴት መፈጸም እንዳለብን በጋራ ተመካክረን አፀደቅን ።
መኖሪያ ቤታችን በብረት ፍርግርግ የታጠረ ነው ። በይበልጥ ማታ ማታ በሩ ስለሚዘጋ መክፈት አይቻልም ። ጨለማን ተገን አድርጐ መንቀሳቅስ እንደ አማራጭ ሊወሰድ ቢችልም በሩ
[page5image33048]
PDF created with pdfFactory trial version www.pdffactory.com
[page5image33904]
ምሽት ላይ በመዘጋቱ ምክንያት የተሻለው ሰዓት በቀን የምናደርገው እንቅስቃሴ ነበር ። ስለዚህ እንቅስቃሴው መጀመር ያለበት በጠዋት እንዲሆን በመወሰናችን አንድ ሁለት እያልን የተለያየ ምክንያት በመስጠት በጠዋት መኖሪያ ቤታችንን ለቀን ወጣን ።
የሰው ኃይላችን በሶስት እንዲከፈል ተወስኗል ። የተለያዩ ሶስት መኪናዎች እያንዳንዱን ግሩፕ እንደሚወስዱ አስቀድሞ ፕላን ተደርጓል ።
በእኔ በኩል ሃሳቤ ተከፋፍሏል ። እያንዳንዷን እንቅስቃሴያችንን በጥርጣሬ ነው የምመለከተው ። የመታፈን ዕድል ሊኖር ይችላል የሚለው ሃሳብ ነፍሴ አስጨንቋታል ። መታፈናችን ለእኛም ፣ ለሌሎች ኢትዮጵያውያኖችም ሆነ ለአጠቃላይ ለትግሉ የሚያመጣው አሉታዊ ጐን ያሳስበኛል ። በሌላ መልኩም ደግሞ እኛን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ኋላ ኋላችን የሚክለፈለፈው ሕውሃት እኛን እጁ በማስገባት ሊፈጥረው የሚችለውን የሞራል የበላይነት በፍፁም አዕምሮዬ ሊቀበለው ፈቃደኛ ሊሆን አይችልም ። በፍፁም ከነነፍሳችን እጃቸው ሊያስገቡን አይገባም እያልኩ በውስጤ ደጋግሜ ቃል እገባለሁ ። በወቅቱ አዕምሮዬ በምን ያህል ፍጥነት ነገሮችን ያወጣና ያወርድ እንደነበረ ፣ የአካባቢያችንን እንቅስቃሴ የማስተውልበት ቅፅበት አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ይገርመኛል ። ነገሮችን ሁሉ በጥርጣሬ እያስተዋልኩ ቢሆንም አማራጭ አልነበረኝምና ማድረግ ያለብኝን ዝም ብዬ ማድረጌን አላቋረጥኩም ።
የግዜ ዑደት አያቆምምና የፍፃሜዋ ሰዓት ደረሰች ። እኔንና አንደኛውን ባልደረባዬን እንዲወስደን የተመደበው መኪና ወደ እኛ እየተቃረበ ሲመጣ ፍጥነቱን አቀዘቀዘ እንጂ ፈፅሞ አልቆመም ። በፍጥነት አንድ ነጭ ሰው ከመኪናው ዘሎ በመውረድና በዚያው ፍጥነት ሁለታችንም ወደ መኪናው እንድንገባ አደረገን ። ሌሎች መኪኖችም በተመሳሳይ ሁኔታ እየመጡ የተቀሩትን ጓደኞቼን በመኪና እያነሱ ተፈተለኩ ።
የጫነን መኪና በፍጥነት ይከንፋል ። መኪናው የሩስያና ቤላሩስ ድንበር ድረስ ለ45 ደቂቃ ሲጓዝ ከጓደኛዬ ጋር አንዲትም ቃል አልተለዋወጥንም ። ይህ ጉዞ ወደ የትኛው የዕድል መስመር እንደሚመራን እርግጠኞች አይደለንም ። ወደ ሕውሃት ቀለበት አይውሰደን እንጂ የትም ብንገባ ግድ አልነበረንም ።
ራሺያና ቤላሩስ ድንበር ስንደርስ መኪናዎቹ በቅፅበት ዋናውን መንገድ በመልቀቅ ወደ መንደሮች ውስጥ በመግባት ጥቂት እንደተጓዝን እንድንወርድ ተነገረን ። ለሚስጢራዊነቱ ተብሎ ስለሚደረገው ነገር አንዳችም መረጃ ስለማይነገረን የሚሉትን ከመፈፀም ውጪ ምንም አይነት ጥያቄ ማቅረብ አልተፈቀደልንም ። በኋላ ግን ከሞስኰ ድረስ ተልኰ እኛን እንዲታደገን አንድ አበሻ በአንደኛው መኪና ውስጥ እንደነበር አስተዋልኩ ። ምንም ጊዜ ሳናባክን አንደኛው ራሺያዊ የለበሰውን ልብስ ሙሉ ለሙሉ አውልቆ ወገቡ ድረስ የሚደርስ
የፕላስቲክ ሱሪና ቦቲ ጫማ እየተጣደፈ ሲያጠልቅ ምን ሊከተል ነው በሚል እንደ ተዓምር አፍጥጠን እየተመለከትነው ነበር ። ወዲያውም በሌላ ፍጥነት ገጀራውን አውጥቶ እንድንከተለው በምልክት መመሪያ ሰጠን ። በዚህን ሰዓት ሁላችንም ምን እየተደረገ ይሆን በሚል እርስ በርሳችን ተያየን ። ሁኔታችንን የተረዳው ከሞስኰ እኛን ለመርዳት የመጣው አበሻ የቤላሩስን ድንበር አቋርጠን ለመውጣት የተሻለው መንገድ ይህ በመሆኑ ሰውየው የሚለንን ያለ አንዳች ማመንታት በተገቢው ፍጥነት ተግባራዊ እንድናደርግ አስረዳን ። ድንበሩን በሰላም እንዳቋረጥንና ወደ ራሺያ ድንበር ከተሻገር ሌላ መኪና እንደሚጠብቀንም ጨምሮ አሳወቀን ። ሁኔታው ግልፅ ሲሆንልን መሪያችንን በልበ ሙሉነት መከተል ያዝን ። መንገዳችን ምን ሊመስል እንደሚችል ከሚመራን ሰው አለባበስና ከያዘው ገጀራ መገመት ችያለሁ ። ሰውዬው እኛን በመምራት በፍጥነት እየተጓዘ ከፊት ለፊቱ ያለውን ጥቅጥቅ ያለ ጥሻ በገጀራው እየቆራረጠ ያፀዳልናል ። እንዲህ እየተከተልነው እያለን ጢሻው ገለል ሲል እስከ ደረታችን የሚያሰጥመን የረጋ ውሃ ውስጥ መሪያችንን ተከትለን ገባን ። መሪያችን ለምን የፕላስቲክ ሱሪ እንደለበሰና ቦቲ ጫማ እንዳጠለቀ አሁን ግልፅ ሆነልን ። አማራጭ የለም እስከ ደረታችን የሚያሰጥመን ውሃ ውስጥ በመግባት የቻልነውን ያክል አካላችንን መጐተት ጀመርን ። ወደ ውስጥ እየዘለቅን ስንሄድ የረጋው ውሃ መጥፎ ሽታና ክርፋት አላስተነፍሰን አለ ። ነፍሳችንን ለማዳን የምናደርገው ጥረት ነውና የመሪያችንን ዱካ ይዘን በብርታት ተከተልነው ። በዚህ ዓይነት ለአንድ ሰዓት ያክል በእግር እንደተጓዝን የቤላሩስን ግዛት ተሻግረን የሩስያ ምድር ላይ አረፍን ። መሪያችን ይህ የቆምንበት መሬት የሩስያ ግዛት በመሆኑና ጉዞው ስላደከመን ተረጋግተን እንድናርፍ አደረገን ።
ሱ-27 ተዋጊ ጀት አውሮፕላን
ከቤላሩስ ለቀን ሌላ አማራጭና የተሻለ ይሆናል በተባለው የሩስያ ግዛት መገኘታችን የተሻለ ተስፋ አለው ብዬ ባምንም መጨረሻችን ምን ሊሆን እንደሚችል ሳላውቅ ልረጋጋ አልቻልኩም ። እረፍት አድርጉ ብንባልም ለአካላችን ካልሆነ
[page6image31144] [page6image31312]
PDF created with pdfFactory trial version www.pdffactory.com
[page6image32168]
በስተቀር አእምሯችንን ከጭንቀት ሊያሳርፍ የሚችል ምዕራፍ ላይ ገና አልደረስንም ።
ትንሽ ከድካማችን ስናገግም ይጠብቃቹሃል የተባልነው መኪና እየቀረበን ሲመጣ አስተዋልኩ ። አንድ ሌላ ሁለተኛ አበሻ አብሮ መጥቷል ። በሶስት መኪና መሆናችን ቀርቶ ሁላችንም በአንድ መኪና ውስጥ እንድንገባ አደረገን ። አበሾቹ ወንድሞቻችን ሕይወታችንን ለማዳን የሚያደርጉልን ጥረት ፣ እየወሰዱት ያሉት አደገኛ ግዳጅ ውስጤን በእጅጉ አበረታኝ ። ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የሚታደጋትና ክፉዋን መስማት የማይፈልጉ ዜጐች በዓለም ዙርያ መኖራቸው በኢትዮጵያዊነቴ ኰራሁ ። ይህ ወንድማችን እየደጋገመ አይዟችሁ ይለናል ። ያበረታታናል ። ቅንነቱና እያደረገ ያለው ከልቡ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻል ነበር ። እናም ጥርጣሬዬ ቀስ በቀስ ከውስጤ እየበነነ ሲሄድና ያ ተለጉሞ የነበረው አንደበታችን ሲከፈት አንድ ሆነ ። በደስታ ማውካካት ጀመርን ። በጉዟችን አቋርጠን የመጣነው መንገድ አስከፊነትና አሁን ያለንበት ሰላማዊ መሬት ላይ እንድንደርስ የረዱንን ሁሉ በአድናቆት ከበሬታ ሰጠናቸው ።
ሞስኰ እንደገባን ለአንድ ወር ከሆቴል ሳንወጣ ተደብቀን ቆየን ። ኢትዮጵያውያኑ ሕይወታችንን ከመታደጋቸውም በላይ እያደረጉልን ያለው እንክብካቤ በቃላት ለመግለፅ ያስቸግራል ። ገንዘባቸውን ፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን እንዲሁም ደህንነታቸውን ጭምር ነበር መስዋዕት እያደረጉልን የነበሩት ። ለእኔ የዕድሜ ልክ ባለውለታዎቼ ናቸው ። ይህንን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለው አሁን ለአለንበት ሰላማዊ አየር ያደረሱን ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ያሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን የዕድሜ ልክ ዕዳ ተሸክሚያለሁ ። በተግባር እነሱ ለሰብዓዊነት የከፈሉት መስዋዕትነት እኔ ተራ ደርሶኝ እስካልከፈልኩ ድረስ በቃላት የምገልፀው ምስጋና ይበቃቸዋል ብዬ አላምንም ። እግዚአብሄር በያሉበት ሰላማቸውን እንዲያበዛ የዘወትር ፀሎቴ ነው ። ወገን ምን ማለት እንደሆነ ፣ የኢትዮጵያዊነት
ጥልቅ
ሚስጢር ፣ የወገን አለኝታነትን በአንድ ላይ በመስዋዕትነታቸው አስተምረውኛልና ።
ከአንድ ወር በኋላ ሞስኰ ወዳለው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኰሚሽን (UNHCR) ቢሮ በመሄድ ማመልከት ነበረብን ። ኬላ ሰብረን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ራሺያ በመግባታችን ምክንያት ጉዳያችንን ላይቀበሉ ይችላሉ ብዬ ሰግቻለሁ ። ይሁን እንጂ እንደፈራሁት ሳይሆን የስደተኛው ኰሚሽን አቤቱታችንን ወዲያ ተቀበለው ። ወዲያውም ወደ ሌላ ሶስተኛ አገር በማሸጋገር በሰላም መኖር የምንችልበት ሁኔታ በአፋጣኝ እንደሚያመቻቹና ረዥም ጊዜም እንደማይፈጅ ሲነግሩን ለአምላኬ ምስጋናዬን አቀረብኩ ።
ሞስኰ ያሳለፍኩት ግዜ በግሌ አስቸጋሪና ብዙ ውጣ ውረዶች የበዙበት ቢሆንም ሕይወት እንዲህ ናትና በቀና ተቀብዬዋለሁ ። እራሳችንን ሙሉ ለሙሉ ለመርዳት ያልደረስን ጥገኞች ነበርንና የሞስኰ ወገኖቻችን እንዲሁም ከአሜሪካ ግዛት የሚደረግልን ድጋፍ ውስጤን ይከብደው ነበር ። እኛን ተከትሎ አየር ኃይሉ በሙያተኞች ያልተቋረጠ የስደት ወጀብ ውስጥ ነበርና እነዚህ ወገኖቻችን እነዚህን ሁሉ ስደተኞች የሚረዱበት አቅም ውስጤን ይበላዋል ። እኛ በቶሎ ነፃ ልናደርጋቸው ይገባል እያልኩ እጨነቃለሁ ። በመሆኑም ከስደተኞቹ ቢሮ ጋር በቅርበት እየተገናኘን ጉዳያችንን መከታተልን ጀመርን ። እግዚአብሄር ደግ ነው ። ጉዳያችን በአፋጣኝ ተከናውኖ ወደ ሶስተኛና ነፃ አገር ያለ አንዳች ችግር መዛወር ቻልን ።
ዛሬ ፈተናው ሁሉ አልፏል ፣ አምላክ በሶስት ልጆች ባርኰኝ ኑሮዬን እየገፋሁ ነው ። ት/ቤት በመግባትም በጤናው ዘርፍ አንድ የመጀመሪያ ዲግሪና ሁለት የማስተርስ ዲግሪ በመያዝ ሙያ ቀይሬ በጥሩ ኑሮ ላይ እገኛለሁ ። አገሬ ግን በልቤ ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንደያዘች አለች ። ሁሌም ሰላሟንና ደህንነቷን እመኛለሁ ። ሕዝቧም ሳይለያይ አንድነቱን ጠብቆ እንዲኖር ፀሎቴ ነው ።
የመጀመሪያ ደረጃ በረራ ስኳድሮን ውስጥ
አየር ኃይልን ሳስብ በእጅጉ እተክዛለሁ ። በዚህ አካሄድ የትም መድረስ እንደማይቻል ሳስብ ለአገሬ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ አምርሬ አዝናለሁ ። እንደዚያ በልጅነት የማልመውን ሙያ አግኝቼ ሳልጠግበው ተገድጄ ማቋረጤ የውስጥ ሕመሜ እንደሆነ አለ ።
[page7image27344] [page7image27512] [page7image27680] [page7image27848] [page7image28016] [page7image28184] [page7image28352]
PDF created with pdfFactory trial version www.pdffactory.com
[page7image29208]
አገራችን የተወሰኑ ሰዎች ብቻ አይደለችም ። እናድርጋትም ቢባል ሊሆን የሚችል ጉዳይ አይደለም ። ይልቁንስ የአገራችን እጣ ፋንታ በመዳፋቸው ውስጥ የወደቀ አካላት አበክረው ሊያስቡበት የሚገባው ጉዳይ በስልጣን ከሚገኘው ደስታና ሃሴት ባሻገር የሕዝብና የአገር ኃላፊነት ሊከብዳቸው ይገባል ።
በመጨረሻም አሁን ላለንበት ሕይወት እንድንደርስ ለረዱንና ለታደጉን አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ሁሉ በቃላት መግለፅ የማልችለውን ምስጋና በድጋሚ ለማቅረብ እወዳለሁ ። ጊዚያቸውን ፣ ገንዘባቸውንና ዕውቀታቸውን መስዋዕት አድርገውልናልና ፈጣሪ ውለታቸውን ይክፈላቸው ።
ከአክብሮት ጋር ፋሲል ማሞ
[page8image5096] [page8image5264] [page8image5432] [page8image5600]
PDF created with pdfFactory trial version www.pdffactory.com
[page8image6456]
   
  •       ​​​​​​​​​​​
                  


                                                                                                      

 ​​​ፋሲል ማሞ - ሚግ 23 ስኳድሮን